ንጉሥ ካሌብ ጻድቅ

ንጉሥ ካሌብ
ጻድቅ ንጉሥ ዘኢትዮዽያ
የተወለደው በ፬፻ዎቹ አጋማሽ
የነገሠበት ዘመን ከ፭፻፰ እስከ ፭፻፴፬
ቀዳሚ ንጉሥ ገብረመስቀል
ተከታይ ንጉሥ አለሜዳ
መንግሥት አክሱም
የዘመኑ ገንዘብ መለዋወጫ
የአክሱማይት ካሌብ የመግዣ ገንዘቦች
የንግሥ ቀን ግንቦት ፳ በኢትዮዽያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
ኦክቶበር 24 በካቶሊክ ቤተክርስቲያን
የሚከበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
በኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
ምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን
ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን


ስመ ንግሡ ዳግማዊ ዐፄ እለ አጽብሃ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ የተሰየመ ይህ የከበረ ጻድቅ የኢትዮጵያ ንጉሥ ካሌብ እግዚአብሔርን የሚፈራውና በፍጹም ልቡ የሚወደው ሃይማኖቱም የቀና ሰው ነበረ ።

ሥጋዊና መንፈሳወዊው ተጋድሎ ክፍል ፩

ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት አምስት መቶ ሃያ ዐራት ዓመት በኋላ በናግራን ሀገር በክርስቲያኖች በአይሁዶችና በአረማውያን መካከል ከባድ ፀብ ተነሣ[1] ። በዚህን ጊዜ ማዝሩቅ ወይም ፊንሐስ የተባለው የሂማሪያው ንጉሥ የአረመኔዎቹንና የአይሁዶቹን ምክር እየተቀበለ ክርስቲያኖቹን ፈጃቸው ። አብያተ ክርስቲያናቱንም ሁሉ አቃጠለ ። ከዚህ ሁሉ በፊት የከሓዲው ንጉሥ ክርስቲያኖቹን የናግራንን ሰዎች ፤ ክርስቶስን ብትክዱት ሕይወታችሁ ይጠበቃል ። ማንኛውም መከራና ሥቃይ ወይም ጥፋት ሊያገኛችሁ አይችልም አለቸው ። እነዚህ ቅዱሳን ሰማዕታት ግን በአምላክነቱ አምነን በስሙ የተጠመቅን እኛስ ክርስቶስን ልንክደው አንችልም ሲሉ በታላቅ ቃል ጮሁ። ዳግመኛም ይህ አላዊ ንጉሥ አምላካችን የምትሉት ክርስቶስ ከእጄ የሚያድናችሁ ይመስላችኋልን? ከዚህ ከሚያስፈራና ከሚያስደነግጥ ሥቃይና መከራ ሊያወጣችሁ ይቻለዋልን? ወደዚህስ ቀርቦ ከእኔ ጋር ይዋጋ ዘንድ ይቻለዋልን አላቸው ።

እኒህንም ቅዱሳን የዚህ አላዊ ንጉሥ አነጋገር አላስደነገጣቸውም ወይም አላስፈራቸውም ። ይልቁንም በመታበዩና በመታጀሩ ኅሊናቸው ስለተነካ በክርስቶስ እምነታችን የጸና ነው ። እርሱ ሁሉ በነፍስና በሥጋ ላይ ለመፍረድ ሥልጣን ያለውን ፍሩት እንጂ በሥጋችሁ ላይ የሞት ፍርድ የሚፈርዱትን አትፍሯቸው ሲል በቅዱስ ወንጌል ነግሮናልና ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ስም መሞትን አንፈራም አሉት ። ከዚያም እሊህ ቅዱሳን ወንዱም ሴቱም ሽማግሌውም ወጣቱም በሙሉ ልባችን በክርስቶስ እምነት የጸና ነው ። ይህ ዓለም ያልፋል ይጠፋል ለኛ ግን ለዘለዓለም የማያረጅ የማይጠፋ ተስፋ ተሰጥቶናል ወይም ተዘጋጅቶልናል እያሉ በተባበረ ድምፅ ጩኸታቸውን አስተጋቡ።

በዚያን ጊዜ የክርስቲያኖቹ መሪ በጣም ክቡር የሚሆንና የዘጠና አምስት ዓመት ዕድሜ ያለው ቅዱስ ሂሩት ከቤተሰቦቹ ጋር በከሃዲው ንጉሥ ፊት ለፍርድ ቀርቦ ሣለ ንጉሡ ፊንሐስ ፊቱን ወደሱ መለስ አድርጎ ሂሩት ሆይ ስማ ይህን ሁሉ መከራ ያመጣብህ በክርስቶስ በማመንህ ነውና እሱን አሁን ፈጥነህ ካደው አለው ።

እግዚአብሔር የመረጠው ቅዱስ ኂሩትም አስቀድመው በመሐላ የገቡትን ቃል የማያከብሩና የተናገሩትን ቃል እንደማያስታውሱ እንዳንተ ያሉ ከሓዲዎች ፈጣሪዬን አልክድም ሲል በድፍረት መለሰለት። በዚህ ጊዜ ከሐዲው ንጉሥ በጣም ተቆጣና ቅዱስ ኂሩትን ወደሚገደልበት ቦታ ወስደው በሰይፍ እንዲገድሉት ጭፍሮቹን አዘዘ ። ክርስቲያኖቹም አባታቸው ወይም መሪያቸው ቅዱስ ሂሩት የከሐዲው ንጉሥ ጭፍሮች ወደሚገደልበት ሲወስዱት ባዩ ጊዜ አባታችን ቅዱስ ሂሩት ሆይ ከሞትህ የሙሽርነት ሠርግ አትለየን። እኛ በክርሰቶስ አምነን ከአንተ ጋር መሞት ይገባናልና አሉት።

አባታቸው ቅዱስ ሂሩትም የእነዚህ ቅዱሳን ሰማዕት ቃላቸው ትክክል ነገራቸውም ዕውነት ፣ ቃል ኪዳናቸውም የጸና መሆኑን ፈጽሞ በተረዳ ጊዜ በእነዚህ ክርስቲያኖች ሕዝቦች ላይ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ በትእምርተ መስቀል እያማተበ ባረካቸው። ከዚህም በኋላ ቅዱስ ኂሩት በንጉሡ ፍርድ ምንም ሳይፈራ በሃይማኖቱ እንደጸና ከቤተሰቦቹ ጋር አንገቱን በሰደፍ ተቆርጦ ሞትና የሰማዕትነት ክብር ተቀዳጀ ። በዚሁ ጊዜ ድማኅ የምትባል ሴት በንጉሡ ጭፍሮች ተይዛ ተገደለችና ከሱ ጋር በሰማዕትነት ዐረፈች ።

እነዚህም ቅዱሳን ሰማዕታት እጃቸው የኋሊት ታሥሮ ሣለ እንደዚሁ በራሳቸው በትእምርተ መስቀል አምሣል አማተቡ። በዚያን ጊዜ ያ አረማዊ ንጉሥ ከሱ ጋር ያለ ፍርሐት በድፍረት በመነጋገራቸው በነዚህ ቅዱሳን ላይ እጅግ ተቆጣ ፤ ስለሃይማኖታቸው ጽናትና ስለልባቸውም ጭካኔ ልቡ በቅናት እንደ እሳት ነደደ ። ከንዴቱም የተነሣ ሰፊና ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ ቆፍረው በውስጡ እሳት ያነዱ ዘንድ አዘዘ ፤ ከዚያም እሊህ ቅዱሳን ፈጣሪያቸው ክርስቶስን አንክድም በማለታቸው በጉድጓድ ውስጥ በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ፈረደባቸውና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእሳት ተቃጥለው ሞቱ። እነዚህም ብዙዎቹ የናግራን ክርስቲያኖች በሚገደሉበት ጊዜ የረዳቶቻቸውን የቍስንጥንያንና የኢትዮጵያን ነገሥታት ስም በጸሎታቸው እያነሱ በሰማዕትነት ሞቱ ።

እኒህም በግፍ የተገደሉት ክርስቲያኖች ቍጥራቸው ሃያ ሺህ ነበር ። ዳግመኛም ይኸው አላዊና ጨካኝ ንጉሥ ፊንሐስ የኤጲስ ቆጶሱን የጳውሎስን አፅም ከመቃብር አስወጥቶ በእሳት አቃጠለው ። እንዲሁም ክርስቲያኖቹን ካሉበት እያደነ በእሳትና በሰይፍ አጠፋቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ በናግራን አገር ስለተፈጁት የክርስቲያን ወገኖች በግፍ የተጨፈጨፉበትን መላእክት የያዘች ደብዳቤ ወደ ኢትዮጵያው አክሱም ንጉሥ ወደ ዓፄ ካሌብ ላከ ። የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ካሌብም ከወርቅ በተሠራው ዙፋኑ ላይ ትቀምጦ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ዙሪያ የጦር አለቆቹና መኳንንቶቹ በክብር አጅበውት ሳለ የሊቀ ጳጳሱ መልእክተኞች ወደ እርሱ ደርሰው የመልእክቱን ደብዳቤ አስረከቡ ። ንጉሠ ዓፄ ካሌብም የመልእክቱን ደብዳቤ ተቀብሎ ነገሩን ወይም ትርጉሙን ከተረዳ በኋላ መልእክተኞቹን ወደአገራቸው በሰላም አሰናበታቸው ።

ከዚያም የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ካሌብ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈቀደልኝስ በግፍ ስለተገደሉት ክርስቲያን ወገኖቼ የማደርገውን አውቃለሁ ሲል በልቡ አሰበ ።

ተጋድሎ ክፍል ፪

፪ ፤ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ካሌብ የናግራንን ሰዎች በግፍ መገደል ከሰማ በኋላ ወደ አባታችን ብፁዕና ቅዱስ የሚሆን ወደ አቡነ አረጋዊ እንዲህ ሲል ላከበት ። ይህ ፊንሐስ የተባለ አረማዊ የናግራንን ሰዎች ደም ያፈሰሰ ቤተ ክርስቲያንን የመዘበረና ያጠፋ ፍጹም የእግዚአብሔር ጠላት ወደሚሆን ሄጀ እዋጋው ዘንድ ተዘጋጅቻለሁ ። ሊቀ ጳጳሱ ጢሞቴዎስም የናግራንን ሰዎችና የሰማዕታቶቿንም ደም ተበቀል ሲል ወደኔ ልኮብኛልና ። ስለዚህ አባቴ ሆይ አንተም በበኩልህ ወደ ጌታዬና አምላኬ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎት አድርግልኝ ። የጻድቅ ጸሎት ትራባለች ፤ ኃይልንም ታሰጣለች፤ በጠላት ላይም ድልን ታቀዳጃለችና ሲል ላከበት ። አባታችን አቡነ አረጋዊም ለንጉሡ መልክተኛ እንዲህ አለው ። ንጉሡን ወደጦሩ ግንባር ሂድ ጠላቶችህን ከእግርህ በታች ያስገዛልህ ተፋላሚዎችህንም እግዚአብሔር በጭፍሮችህ እጅ ይጣላቸው። ለአንተም ታላቅ ግርማ ሞገስ ይስጥህ ። በሰላም ይመልስህ ብለህ ንገረው አለውና እርሱም ይህንኑ ነገረው ። የኢትዮጵያው ንጉሥ ዓፄ ካሌብም ለጦርነት ጉዞውን ከመቀጠሉ በፊት ወደቤተ ከርስቲያን ሄዶ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ ፣ ማቅ ለብሰ። አቅርንተ ምሥዋውን እየተማፀነ ዓይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ እያለ ጸለየ ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ በሰማይም በምድርም ያለውን ሁሉ የፈጠርክ እልፍ አእላፍ መላእክት የሚገዙልህ ኪሩቤልና ሱራፌል የሚያመሰግኑህ የካህናት ፈጣሪያቸው ። አቤቱ የጌቶች ጌታ የነገሥታትም ንጉሥ የምትሆን የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት ብርሃናትን የፈጠርክ ሰውን ሁሉ ከኃሣር ወደ ዘለዓለም ክብር ይመልስ ዘንድ አንድ ልጅህን ወደኛ የላክኸው ። አቤቱ የአባቶቻችን ፈጣሪያቸውና አምላካቸው ሆይ እኛን ስለማዳን ፍጹም ሰው በሆነው ልጅህ ምክንያት ይህ ከሐዲ ፊንሐስ ያደረገውን እነሆ አይተኸዋል። ወገኖችህንም እንደ በግ እንዳረዳቸውና አብያተ ክርስቲያናትህንም እንዳቃጠለ ተመልክተነዋል። አቤቱ እነሆ ከዚህ ወጥቼ ይህን ያንተንና የኛንም ጠላት ከሐዲ አይሁዳዊ በአንድ ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል አጠፋዋለሁ ። ስለሆነም አቤቱ አታሳፍረኝ ስለ አንተ ስለፈጣሪዬና ስለ ክርስቲያን ወንድሞቼ ቅናት አድሮብኛልና ። አቤቱ ቦኃጢአቴ ብዛት ጸሎቴን የማትቀበል ልመናዬን የማትሰማ ከሆነ ግን በዚች በቆምኩባት ቦታ በአሁኑ ሰዓት ሕይወቴ ታልፍ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን ። አቤቱ ጌታዬና አምላኬ ሆይ ፤ ርስትህ የምትሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ስምህን በማያውቁ ጠላቶችህ እጅ አሳልፈህ አትስጣቸው ሲል አጥብቆ ለመነ ። ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ካሌብም ታላቅ ጻድቅ ሰው ነበር ከምድር ነገሥታት ወገን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ እያለ ማንም እንደሱ ድንቅ ተአምራት ያደረገ የለም ። ከሁሉም በፊት የዑር አገር ሰዎች ባመፁበት ጊዜ የሀገሪቱ ሰዎች የጦሩን መትመምና ግስጋሤ አይተው እንዳይሸሹና እንዳያመልጡ እግዚአብሔር በምድር ውስጥ መንገድ ከፈተለት ። የመንገዱም ርዝመት መጠን ለጐበዝ ተራማጅ ወይም ፈጣን ሩዋጭ ሰው ሦስት ቀን የሚያስኬድ ጐዳና ነበር ። ከዚያም እግዚአብሔር በመሬት ውስጥ በከፈተለት መንገድ ገብቶ ገሥግሶ ድንገት ደረሰና ደመሰሳቸው አጠፋቸውም ። ከነሱ አንድ ስንኳ አላስቀረም ። ሀገሪቱንም በእጁ አገባት እስከ ዛሬም ድረስ አለች ።

ተጋድሎ ክፍል፫

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ይኸው የኢትዮጵያ ንጉሥ እፄ ካሌብ ሰባ ሺህ የሚደርሰውን ጦሩን አስከትቶና አዘጋጅቶ ቀድሞ ወደ አሰበበት ወደ የመን በመርከብ ተጓዘ ። ከዚያም የኢትዮጵያው ንጉሥ ካሌብ ከመርከብ ሲወርድ ጠብቆ ከሐዲው ንጉሥ ብዙ ጦር አሰልፎ ካሌብን ወጋው ። በመካከላቸውም የሚደረገው ጦርነት በጣም የበረታ ሆነ ። ያን ጊዜም ካሌብና የጦር ሠራዊቱ በጦርነቱ መካከልና በጠላቶቻቸው ፊት እጅግ በረቱ ። የከሐዲውን ንጉሥ ሠራዊትም አሸንፈው በታተኗቸው ። ይልቁንም ካሌብ እራሱ ያን ከሐዲ ንጉሥ ፊንሐስን ገጠመውና በፈረሱ ላይ እንደ ተቀመጠ በጨበጣ በጦር ወግቶ ገደለውና ወደ ባሕር ገልብጦ ጣለለው። ያም ከሐዲው ንጉሥ ከዚያው ሰጥሞ ሞተ ፤ ሚስቱም በዚሁ ጊዜ ተማረከች ። ከዚያም በኋላ አፄ ካሌብ ዛፋር ፣ ወደምትባለው ወደ ሳባ ከተማ በታላቅ ግርማ ገስግሦ ሄደ ። የከተማውንም ጠባቂዎች አሸንፎ ገብቶ፣ ከተማዋን ያዘ ። ይህም የተደረገው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላ በአምስት መቶ ሃያ አምስት ዓመተ ምሕረት ላይ ነው ። ፲፬ ፣ ከዚህም በኋላ በዛፋር ከተማ ውስጥ እየተዘዋወረ በክርስቲያኖቹ እልቂት ዕለት ደም በማፍሰስ የተባበሩትን የከሐዲውን የፊንሐስን ሹማምንት እያስፈለገ አስያዘና በአደባባይ በማስገደል በሀገረ ናግራን የተፈጁትን ክርስቲያኖች ደማቸውን በሚገባ ተበቀለ ። የተረፉት ክርስቲያኖችም ከሸሹበትና ከተሸሸጉበት ወደ ቀደመ ቦታቸው ተመለሱ ። ኢትዮጵያዊው ንጉሥ አፄ ካሌብም የድል አድራጊነትን አክሊል እንደ ተቀዳጀ ለእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ መልእክት ላከ ። ሊቀ ጳጳሱም ወደ ቍስጥንጥንያው ንጉሥ ይህንኑ የደስታ መልእክት አስተላለፈና በሁሉም ዘንድ ታላቅ ደስታ ተደረገ በዚያን ጊዜ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አንድ ኤጲስ ቆጶስ ሾሞ ወደ ብሔረ ሳባ ላከ። ኢትዮጵያዊው ንጉሥ አፄ ካሌብም የአይሁዱ ንጉሥ በሚገዛበት በዚያ ግዛት ሁሉ ቤተ ክርስቲያን አሣነፀ ። ለቤተ ክርስቲያኑም መሠረት እራሱ ዓፄ ካሌብ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ሲያስቆፍር ሰነበተ ። ከዚያም ታላቅ በዓል አድርጐ እግዚአብሔርን አመሰገነው ። ያ የክርስቶስ ጠላት አረማዊ ንጉሥ የመዘበራትንና ያጠፋትን ቤተ ክርስቲያን በናግራን ሀገር ላይ እንደገና አሣነፀ ። ከሳባ ሀገር የማረከውን ንብረት ገንብና ጌጣ ጌጥ ሁሉ ለቤተ ከርስቲያኗ ክብር ሰጠ ። ከዚያም ለዚያች ለብሔረ ሳባ ስሙ አብርሃ የሚባል ብልህና ዐዋቂ ሰው መርጦ ሾመላቸው ። ቀጥሎም ገዥውን አብርሃንና ኤጲስ ቆጶሱን የሚጠብቁ ዓሥር ሺህ የጦር ሠራዊት መደበላቸው ። ከዚህ በኋላ ወደ ሀገሩ ወደ አክሱም በፍጹም ደስታና ፍሥሐ በድል አድራጊነት በሰላም ተመልሶ ገባ ። የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ የክርስቲያን አምላካቸው እግዚአብሔር በዚህ ኃያልና ተጋዳይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ በዓፄ ካሌብ እጅ ያደረገውን ድንቅ ሥራ ተመልከቱ። ይህ ዓፄ ካሌብ የአክሱምን መንግሥት የጥንት ግዛቱን በድል አድራጊነት በማስመላሱ የታወቀ አስፈሪና ገናና ንጉሥ ሆኗልና ። ይልቁንም በናግራን የተፈጁትን ክርስቲያኖች ደም በመበቀሉ በእስክንድርያ በቍስጥንጥንያ በአንጾኪያና በሮም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ኀዘናቸው ወደ ደስታ እንዲለወጥ አድርጓልና። ይህ አማናዊ ንጉሥ ከዓረብ ሀገር ፈጽሞ ሊጠፋ የነበረውን የክርስትና አምልኮ ወደ ጥንት ቦታው መልሶ አቃናው። በቃል ኪዳን ጓደኝነት አንድ ሆነው በነበሩት በአይሁድና በፋርስ ሕዝብ ላይ አደጋ ጥሎ ከዐረብ አገር ግዛታቸውን አስወግዶ ክብራቸውን አሳንሶ እነሱንም አባሮ የራሱን አስተዳደር ተክቶና ገናንነቱን አሳውቆ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት አደላደለ ። ስለዚህ ይህ ታላቅ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ካሌብ በምሥራቅ በቍስጥንጥንያና በአረቦችም በቤተ መንግሥቱም በቤተ ክህነቱም በሁሉም ዘንድ ታላቅ ስመ ጥርና ሰፊ ታሪክ ያለው ሆነ ። ክብሩም ከተጋዳዮች ቅዱሳንና ከታላላቅ ሰማዕታት ክብር ጋር የተካከለ ሆነ ። ስለዚህም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመታሰቢያውን በዓል በጥልቅ ስሜት ታከብራለች ። የምታከብረውም የኛ ቤተ ክርስቲያን ብቻ አይደለችም ። ነገር ግን የሮማም ቤተ ክርስቲያን የመታሰቢያውን በዓል ከሌሎቹ አሸናፊዎች ሰማዕታት በዓል ጋር በማስተካከል በጥቅምት ሃያ ሰባት ቀን በታላቅ ክብርና በብዙ ደስታ ታከብረዋለች እንጂ

መንፈሳዊ ብቃት

የኢትዮጵያው ንጉሥ አፄ ካሌብ በናግራን ሀገር ጦርነት ድልን ተቀዳጅቶ ከተመስሰ በኋላ ኃይልና መጠጊያ ረዳቴና አዳኜ የሚሆን እግዚእብሔርን ምን አድርጌ ላስደስተው ሲል አሰበና የዚህን ዓለም መንግሥት ተድላ ደስታ ንቆ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ አንዲት የውሃ መንቀልና አንዲት ምንጣፍ ብቻ ይዞ አባ ጰንጠሌዎን ገዳም አጠገብ ከሚገኝ ዋሻ ወስጥ ገብቶ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ ለመቀመጥ ወሰነ ። አባ ጰንጠሌዎንንም አመንኵሰኝ አለውና የመላእክትን አስኬማ አልብሶ አመነኰሰው ። ዳግመኛም ከዋሻ ወይም ከገዳም ወጥቶ ዓለምን በዓይኑ ላለማየት ማለ ቃል ኪዳንም ገባ። ቤተ መንግሥቱን ለቆ ወደ ምናኔ በሄደበት ጊዜ ዋጋው እጅግ የከበረውንና በነገሠ ጊዜ የጫነውን የወርቅ ዘውዱን ከጌታችን አንቀጸ መቃብር ላይ ይሰቅልለት ዘንድ ከአደራ ደብዳቤ ጋራ ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ለአባ ዮሐንስ ላከለት። ዳግመኛም ንጉሥ ዓፄ ካሌብ አባቴ ሆይ በአንተ ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ከጦርነቱ በሰላም ተመልሻለሁ አሁንም የክርስቶስን አርዑተ መስቀል ተሽክሜአለሁና እግዚአብሔር ለፍጻሜው ያብቃህ እያልክ ስለኔ ጸልይልኝ ሲል ወደ አባታችን ወደ አቡነ አረጋዊ ላከበት ። ስለዚህም ነገር አባታችን አቡነ አረጋዊ በጣም ተደስቶ ልጄ ሆይ መልካሙን የበለጠውን አድርገሃል። አሁንም እግዚአብሔር የፈቀድከውን ነገር ሁሉ ይፈጽምልህ በለው አለው። መልክተኛውም ይህን ከሰማ በኋላ ከአባታችን ከአቡነ አረጋዊ ዘንድ በረከትን ተቀብሎ ወደ መጣበት ተመልሶ ሄደ። ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዓጼ ካሌብ ይህን ዓለም በመናቅ በበረኃ በዋሻ ዐሥራ ሁለት ዓመት በጾምና በጸሎት በብዙ ተጋድሎ ሲኖር በግንቦት ሃያ ቀን ዐርፎ እስከ ዘለዓስሙ ድረስ የማያልፍ ሰማያዊ ክብርን ወረሰ ።

የተወደዳችሁ ወንድሞች ጻድቅና ትሑት የሚሆን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ካሌብ በፈጣሪው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ያደረገውን ድንቅ ሥራ እስኪ ተመልከቱ ። የሱና የፈጣሪውን ጠላቶች ዓላውያን ነገሥታት ባጠፋና የጦር ኃይላቸውን በደመሰሰ ጊዜ በኃይሉ አልተመካምና። ከጦር ሜዳም በድል አድራጊነት በተመለሰ ጊዜ ጐልያድን እንደ ገደለ እንደ ዳዊት ዘፋኞች ይዘፍኑለት ወይም ያሞግሱት ዘንድ አልወደደም። ነገር ግን የዚህን ዓለም መንግሥት ንቆ ወደ ምድረ በዳ ወይም በረሃ ገብቶ በትንሽ ዋሻ ውስጥ መኖርን ወደደ እንጂ ። ሎጥ ከሰዶምና ከገሞራ በሚወጣበት ጊዜ መላእክት እስኪያቻኩሉት ድረስ ወዲያ ወዲህ በማለት ለመዘግየት አልፈለገም ። የጨው ዓምድ እንደሆነችው እንደ ሎጥ ሚስትም ክብሩን በማሰብ ፊቱን ወደ ኋላው አልመለሰም ።

እንግዲሀ ከኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ከካሌብ በስተቀር በሚታየው ክብር የማይታየውን ክብር ለውጦ በቆራጥነት ይህን ዓለም ንቆ ሁለተኛ ላለመመለስ ወደፊት ገሥግሶ በረኃ የገባ ማነው እሱ? እኛም እግረ ኅሊናችንን በቀና ጐዳና ይመራልን ዘንድ እግዚአብሔርን እንለም ነው ። ርስተ ወመንግሥተ ሰማያትንም ለመውረስ ዕድል ፈንታችንን ከቅዱሳኖቹጋር ያድርግልን ለዘለዓለሙ አሜን ።