ዛጔ ሥርወ-መንግሥት
የአገው ሥርወ-መንግሥት
"አገው ልቡ ዘጠኝ፤ ስምንቱን አኑሮ በአንዱ አጫወተኝ ለምን ይባላል?"
ከታሪክ ስንነሳ የአገው ህዝብ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሐይማኖቱ ጠንካራ አማኝ ና በሐይማኖት ጉዳዮች ላይ በፅናት በመቆም ሚስጥራትን የሚጠብቅ ነው፡፡ በሐይማኖት ጉዳዮች ላይ ቀልድና ዋዛ ፈዛዛ አይወድም፡፡ ከእንግዳ ሰዎች ወይም ከባዕድ ጋር ሲገናኝ ደግሞ በቶሎ ተግናኝቶ አይመሳሰልም ፤ አይደባለቅም ፡፡ ነገር ግን እንግዳውን በአግባቡ እያስተናገደ በልቡ ግን ይመረምረዋል፡ ያጠናዋል፡ የምን እምነት ተከታይ እንደሆነ ፤ ኑሮው አና ባህሉ አንዴት እንደሆነ ለማዎቅና ለመጠንቀቅ ይሞክራል፡፡ ወዲያውም እውነተኛ አማኝና ክርስቲያን መሆኑን ሲያረጋግጥ እንደ ርግብ የዋህ ይሆንለታል ማለት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዘመነ ዛጉዌ ሥርወ-መንግስት
ዛግዌ የሚለዉ ስያሜ የሥርወ-መንግሥቱ ተዋናዮች (Actors) የነገደ አገው ተወላጆች ስለኾኑ የአገው መንግሥት ለማለት ’’ዘአገው’’ ከሚለው ቃል የተወሰደ ነው፡፡ ለዛግዌ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት የዘር ግንድ መሰረት የሆነው መራ ተክለሃይማኖት የአክሱም መንግሥት ካከተመ በኋላ በትረ መንግሥቱን ጨብጦ መናገሻ ከተማዉን ወደ ላስታ በማዞር በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እነዲጀመር ምክንያት ሆኗል፡፡ ከመራ ተክለሃይማኖት ጀምሮ ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ዐሥራ አንድ የዛግዌ ነገሥታት ኢትዮጲያን እንደ አስተዳደሩ ትውፊታዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከነዚህም መካል አራቱ ክህነትን ከንግሥና ጋር አስተባብረው የያዙ እና በቤተክርስቲያን ቅድስናቸዉ የሚታወቁ ናቸው፡፡
ካህናት ነገሥታት የሚባሉት
ከአስራአንዱ የዛግዌ ሥርወ-መንግሥት ነገሥታት መካከል ቀደም ብለን እንደገለፅናቸው፣ ካህናት ነገሥታት በመባል የሚታወቁት አራት ናቸው፡
፩) ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ
፪) ቅዱስ ሐርቤ(ገብረ ማረያም)
፫) ቅዱስ ላሊበላ
፬) ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ናቸው፡፡
እነዚህ ነገሥታት ለክርስትና እምነታቸዉ የነበራቸዉ ፍቅር፣ያደረጉት መስዋዕትነትና ውለታ ማንነታቸዉን ይገልፃቸዋል፡፡ በርግጥ ሁሉም የዛግዌ ነገሥታት ክርስቲያኖች ስለነበሩ በዮዲት ጉዲት የጥፋት ዘመቻ ምክንያት፡
-ተመናምኖ የነበረዉን ክርስትና እንደገና እንዲያንሠራራ ማድረጋቸው
-ተስፋ የቆረጠዉን ሕዝበ-ክርስቲያን እንዲፅናና፣ማድረጋቸው
-የተቃጠሉ መጽሐፍት እንደገና እንዲፃፉና ማድረጋቸው እና
-የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንደገና እንዲሰሩ ያደረጉት ጥረት፤
በኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ታሪክ የሚረሳ አይደለም፡፡ ከሁሉም በበለጠ እነዚህ አራቱ ነገሥታት ሙሉ ሕይወታቸውን ለመንፈሳዊ ነገር አዉለዉ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ፣ በፅድቅ ሥራቸዉ ኹሉ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አራያ በመሆን የክርስትና ሃይማኖት እንዲከበር፣ እንዲስፋፋና እንዲጠናቀር በማድረግ በፍፁም ተጋድሎ ቤተክርስቲያንን ያገለግሉ ስለሆነ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዉለታቸዉን ባለመዘንጋት የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ ትጠራቸዋለች፡፡ ስለነዚህ ቅዱሳን ነገስታት በገድላቸዉ፣በታሪክ ነገስታቸዉና በስንክሳር ከተዘገበዉ ሌላ ትተውልን የኼዱት አስደናቂ ቅርሶቻቸዉ ማንነታቸውን ይነግሩናል፡፡ በይተለይ በነዚህ ቅዱሳን የታነፁ አብያተ ክርስቲያናት ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያገኙና መንፈሳዊ ምግባራቸዉንና የቅድስና ሕይወታቸውን አጉልተዉ በማሳየት አራያ የሚሆኑን ናቸዉ፡፡ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ክፍል-2 ገጽ 43)
የአራቱን ቅዱሳን ነገስታት ዘመነ መንግሥት ልዩ የሚያደርገዉ ከሁሉም በላይ ቤተክርስቲያን የነበራት ክብርና ድጋፍነበር፡፡ ነገስታቱ ራሳቸዉ ካህናት ፍፁም መንፈሳዊያን ስለነበሩ ለቤተክርስቲያን በነበራቸዉ ታላቅ ፍቅር ሌላዉም ህዝበ ክርስቲያን አርአያነቱን በመከተል ለቤተክርስቲያን ትልቅ ድጋፍ ነበረዉ፡፡እነዚህ ነገስታት አብያተ ክርስቲያናትን ከማሳነጽ ሌላ ለበርካታ ገዳማትና አድባራት ተጨማሪ መተዳደሪያ ይለግሱ ነበር። ከምንም በላይ ግን የታላቋ ኢትዮጵያ የስልጣኔ ምልክት ተደርገው የሚወሰዱ የ ኪነጥበብ ስራዎች በዛግዌ ስርወ መንግስት ዘመን የጸሩ ስለመሆናቸዉም ብዙ መጻህፍት ያትታሉ፤ ከነዚህም ዋነኛዎቹ የ ቅዱስ ላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስቲያናት ይጠቀሳሉ።