ልብነ ድንግል
- «ዓፄ ልብነ ድንግል» ወዲህ ይመራል። ለቤተ ክርስቲያኑ፣ አጼ ልብነ ድንግል ይዩ።
==
ዓፄ ልብነ ድንግል | |
---|---|
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ | |
ግዛት | ከነሐሴ ፲ ቀን ፲፬፻፺፱ እስከ ነሐሴ ፴ ቀን ፲፭፻፴፪ ዓ.ም. |
በዓለ ንግሥ | ግንቦት ፰ ቀን ፲፭፻ ዓ.ም. |
ቀዳሚ | ዓፄ ናዖድ |
ተከታይ | ዓፄ ገላውዴዎስ |
ባለቤት | ንግሥት ሰብለ ወንጌል |
ሙሉ ስም | አንበሳ ሰገድ ዳግማዊ ዳዊት |
ሥርወ-መንግሥት | ሰሎሞን |
አባት | ዓፄ ናዖድ |
እናት | ወ/ሮ አትጠገብ ወንድበወሰን |
የተወለዱት | በደብረ ዳሞ፣ ትግራይ |
የሞቱት | ነሐሴ ፴ ቀን ፲፭፻፴፪ ዓ.ም. |
የተቀበሩት | አባ አረጋዊ |
ሀይማኖት | የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና |
==
ዓፄ ልብነ ድንግል (የዙፋን ስም "አንበሳ ሰገድ" ወይም ዳግማዊ ዳዊት) ከነሐሴ ፲ ቀን ፲፬፻፺፱ እስከ ነሐሴ ፴ ቀን ፲፭፻፴፪ ዓ.ም. የነገሱ ሲሆን የተወለዱትም በ1501 እ.ኤ.አ. ነበር። የኢትዮጵያና አዳል ጦርነትም የተጀመረው በኒህ ንጉስ ዘመን በ1528 እ.ኤ.አ. ነበር። ሚስታቸውም ሰብለ ወንጌል ትባል ነበር።
ዓፄ ልብነ ድንግል የዓፄ ናዖድ ልጅ የዓፄ በአደ ማርያም የልጅ ልጅ ናቸው። ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብም ቅድመ አያታቸው ናቸው። ዓፄ ናዖድ ፲፫ ዓመት ገዝተው ሲሞቱ በ፲፭፻ ዓ.ም. ዓፄ ልብነ ድንግል ገና የ፲፪ ዓመት ወጣት እያሉ ነገሡ። ስመ መንግሥታቸውም ወናግ ሰገድ ተባለ። ወናግ ማለት በኦጋዴን (ሱማሌ) ቋንቋ አንበሳ ማለት ነው። የግዕዙን ወይም የአማርኛውን ቋንቋ «አንበሳ ሰገድ»ን ትተው በኦጋዴን ቋንቋ ወናግ ሰገድ የተባሉበት ምክንያት ምናልባት ያን ጊዜ በይፋትና በፈጠጋር ያለውን ግዛት የሚያውኩ ያዳልና የሱማሌ ተወላጆች ስለሆኑ እነሱ በሚያውቁት ቋንቋ ተሰይሞ ለማስፈራራት ይሁን ወይም የነሱ ገዥ ጭምር መሆናቸውን ለማስታወቅ ይሁን ወይም ከአባታቸው ከዓፄ ናዖድ ስመ መንግሥት (አንበሳ ሰገድ) በትርጉም ቢቀር በአጠራር እንዲለያይ ይሁን በትክክል አይታወቅም። ዓፄ ልብነ ድንግል ራሳቸው ለፖርቱጋል ንጉሥና ለሮማ ሊቀ ጳጳስ በጻፉዋቸው ደብዳቤዎች ላይ «ስሜ ልብነ (ዕጣን) ድንግል ትርጓሜው ድንግል ያበራችለት ይሄም ስም የተሰጠኝ ቅድስት ጥምቀትን በተቀበልኩበት ቀን ነው፤ በነገሥኩ ጊዜ ደግሞ ዳዊት ተባልኩኝ» ስለሚል በዳዊት ላይ ተጨማሪ ወናግ ሰገድ ሆኖ በሁለት ስመ መንግሥት ይጠሩ ነበር ማለት ነው።
ዓፄ ልብነ ድንግል በነገሡ ጊዜ ወጣት ስለነበሩ በመንግሥቱ ሥራ እናታቸው እቴጌ ናዖድ ሞገሳ የአያታቸው የዓፄ በአደ ማርያም ባለቤት እቴጌ እሌኒ በሞግዚትነት ያግዟቸው ነበር። እነራስ ወሰን ሰገድና እነራስ ደገልሃን የመሳሰሉትም ታላላቅና ታናናሽ መኳንንት የመንግሥቱ የሥልጣንና የሥራ ተካፋይ ነበሩ።
በመጀመሪያ፣ የዓፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት የሰላምና የደስታ ቢሆንም የመጨረሻ ጊዜያቸው በግራኝ መነሳት ምክኒያት የጦርነት፤ የሁከት፤ የመከራና የስደት ጊዜ ሆኖባቸዋል። ከፖርቱጋል መንግሥት በቀጥታም ሆነ በእቴጌ እሌኒ በኩል ቢወዳጁ የጀመሩት ወዳጅነት ለጊዜው ጠቡን አጣደፈው እንጂ ከወረራ ሊያድናቸው አልቻለም።
ዋቢ መጽሐፍ
- ተክለ ጻድቅ መኵሪያ፤ ፲፱፻፶፫ ዓ.ም.፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ
|